በሱማሌ ክልል በተዘጋጀው የክልሉ የቤተሰብ ህግ ላይ ምክክር ተካሄደ

(ጅግጅጋ፣ ነሐሴ 17/2015 ዓ.ም) የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በሱማሌ ክልል ቀደም ሲል የተዘጋጀው የቤተሰብ ህግ መሻሻል፣ መጽደቅ እና በስራ ላይ መዋል በሚችልበት አግባብ ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ እና አጋር አካላት በጅግጅጋ ከተማ የምክክር መድረክ ተካሂዷል። የመድረኩ ዓላማ በህጉ ዳግም መታየት ያለባቸው እና በቀጣይ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮችን ለመለየትና የቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ እንደሆነ ተገልጿል።
በመድረኩ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ክብርት ወ/ሮ አለሚቱ ዑመድ እንደገለፁት፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ ለሴቶች እና ህጻናት መብቶች መከበር ጉልህ አስተዋጽዖ ያበረከቱ የተለያዩ አለም አቀፍ እና አህጉራዊ ስምምነቶችን እንዲሁም ልዩ ልዩ ፕሮቶኮሎችን ተቀብላ ከማጽደቅ ባሻገር ሌሎች ደጋፊ የህግ ማዕቀፎችን በመንደፍ ተፈጻሚ እንዲሆኑ አስተዳደራዊ እርምጃዎችን ስትወስድ ቆይታለች ብለዋል። የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ ጸድቆ በአብዛኛው ክልሎች በስራ ላይ መዋሉን ያስታወሱት ሚኒስትር ደኤታዋ በተመሳሳይም በሱማሌ ክልል ካለው ነባራዊ ሁኔታና ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ጋር በተጣጣመ መልኩ የቤተሰብ ህጉ ተሻሽሎ እንዲዘጋጅና በቀጣይ ጸድቆ በስራ ላይ እንዲውል ለማስቻል ከክልሉ የሚመለከታቸው ባለድርሻና አጋር አካላት እንዲሁም ከሌሎች የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር በቅንጅት ሰፊ ስራ ሲሰራ መቆየቱ አስታውቀዋል።
በክልሉ የተዘጋጀው የቤተሰብ ህግ ከሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች አንጻር ስላለው አንድምታ የጋራ ግንዛቤ እንዲያዝበት ለማስቻል እንዲሁም የተለዩ አጀንዳዎችን በውይይት ለማዳበርና ተጨማሪ ግብዓት ለማሰባሰብ ታስቦ መድረኩ መዘጋጀቱንም አያይዘው ገልጸዋል ።
በመድረኩ ቀደም ብሎ በክልሉ ምክር ቤት ፀድቆ የነበረው የቤተሰብ ህግ ከህገ-መንግስቱና ከሰብዓዊ መብት አንፃር እንዲታዩ አስተያየት በተሰጠባቸው እንዲሁም ከሀይማኖትና ባህል አኳያ መጣጣምን የሚጠይቁ የተለዩ ጉዳዮችን አስመልክቶ በክልሉ ፍትህ ቢሮ እንዲሁም ደግሞ የቤተሰብ ህግ ከሴቶችና ህፃናት ሰብዓዊ መብቶች በሚል ርዕስ በሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ተወካይ በኩል ቀርቦ ግንዛቤ እንዲያዝበት ተደርጓል።
በቀረቡት ሰነዶች ላይ ህጉን ለማዳበር የሚረዱ ጠቃሚ ግብዓቶችና እና ምክረ ሃሳቦችን የተንሸራሽሩ ሲሆን በመጨረሻም በክልሉ ሊታዩና ሊሻሻሉ የሚገባቸው ጉዳዮች በመለየት በኩል ውጤታማ እንደነበር እንዲሁም በቀጣይ የቤተሰብ ህጉን ከሀይማኖት፣ ከባህል፣ ከሰብዓዊ መብትና ከህገ-መንግስቱ ጋር በማይጣረስ መልኩ መሻሻል የሚገባቸውን ለማየት እንዲያስችል በክልሉ በየደረጃው የሚመለከታቸው አካላትን ያቀፈ የጋራ ኮሚቴ በማዋቀር ግልጽነት ያልተፈጠረባቸውን ጉዳዮች የማጥራት ስራ ለመስራት ስምምነት ላይ ተደርሷል ። በመድረኩ ከፌዴራል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና ማህበራዊ ልማት የባህልና ስፓርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ ከህግና ፍትህ ቋሚ ኮሚቴ፣ ከሴቶች ተመራጭ ኮከስ፣ የሴቶችና ህፃናት፣ የማህበራዊና የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታዎች እንዲሁም የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ኡላማዎች፣ ከተለያዩ ተቋማት የተወከሉ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
በመድረኩ ላይ የኮሚቴው አባል በመሆንም ሆነ የፋይናንስ ድጋፍ ላደረጉት የአጋር አካላት ለUN-Women, Save the Children Ethiopia እና Norwegian Church Aid ከፍተኛ ምስጋና የተቸራቸው መሆኑ ታውቋል።

    Subscribe to our blog and get the latest updates straight to your inbox.